ማህበረሰብንና አትክልተኛን አመሳሰልኳቸው

አትክልተኛ /አትክልት ተንከባካቢ/ ተመሳሳይ አትክልቶች በቅለው ለማየት አስቦ ተመሳሳይ ዘሮችን ይዘራል፡፡ የተዘሩት ዕፅዋትም እንደ አትክልተኛው የእንክብካቤ እና አጠቃላይ አያያዝ ሁኔታ ይበቅላሉ፣ በቅለውም የታሰበላቸውን ውበት የመስጠት ግዴታ ይወጣሉ፡፡ ታዲያ ውበታቸው የሚወሰንላቸው በአትክልተኛው ፈቃድ ነው፡፡ አትክልተኛው ያልወደደው ቀለም ወይም ቁመት ከያዙ በሌሎች አትክልቶች ዘንድ ያስቅባቸዋል፣ ወዲያውኑም ይቆርጣቸዋል፡፡ በምንም ዓይነት አኳኋን ከአብዛኛው አትክልቶች መለየት የለባቸውም ብሎ ስለሚያስብ ለተለዩት አትክልቶች የሚያሳየው አንዳች ርህራሄ የለም፡፡ በዚህም ሁኔታ አትክልቶቹ ቁመታቸውና መልካቸው እንደተወሰነላቸው ይኖራሉ፡፡ ኖረው ኖረው እድሜያቸው እንዲቀየሩ ስለሚያስገድድ አትክልተኛው የነበሩትን አጥፍቶ በአዲስ አትክልቶች ይቀይራቸዋል፡፡

ምናልባት ዕድል ቀንቷቸው አትክልተኛው በጊዜ ሂደት የአንዳንድ አትክልቶች ቁመት ከሌሎቹ ተለይቶ ማደግንና የተለየ ቀለም መያዝ ሌሎችም ተመሳሳይ ነገር ቢኖራቸው በሚሰጡት ውቨት ላይ ምንም ችግር እንደማያመጣ ከተገነዘበ የተቀሩት ብዙዎቹ አትክልቶችም እንዲያድጉ ተጨማሪ እንክብካቤ ያደርገላቸዋል፡፡ አጫጭር የነበሩ አትክልቶች ድሮ ከሚደረግላቸው ተጨማሪ እንክብካቤ ሲያገኙ ካደጉት አትክልቶች ጋር ለመስተካከል ብዙ ጊዜ አይጨርስባቸውም (መጀመሪያ ላይ ያደጉት አትክልቶች ከወሰደባቸው ጊዜ ባነሰ ያድጋሉ-የተለየ እንክብካቤ ስለሚደረገላቸው)፡፡ እንግዲህ ከዚህ የምንረዳው ሁሉም አትክልቶች ድሮ ከነበራቸው ቁመት አዲስ እና ትልቅ ቁመት እንዲያገኙ የአንዳንድ አትክልቶች ተለይቶ ማደግ፣ የእነዚህ አትክልቶች በአትክልተኛው ዘንድ አለመወደድ ከፍ ሲልም መቆረጥን ማስተናገድ ግድ ይላቸዋል ምክንያቱም አትክልተኛው የአትክልቶቹን ቁመት ገና ሲዘራቸው ዠምሮ ስለወሰነ ማንም አትክልት ተለይቶ ያድግ ዘንድ አይፈቅድለትምና፡፡

ማህበረሰብም ሰዎችን ይወልዳል፡፡ የተወለዱት አዳዲስ ሰዎች በወላጆቻቸው፣ በአያቶቻቸው እና በቅደመ አያቶቻቸው ዘንድ ገዢ የነበሩ ማህበረሰብ ተኮር ህግጋት እና አስተሳሰቦችን ይከተሉ ዘንድ ያስተምራቸዋል፡፡ ጎጂ ያላቸውንም ነገሮች እንዲሁ የሰይጣንነት ትርጉም እየሰጠ አዳዲሶቹ ሰዎች የተለየ መልክ እንደዳይዙ ያደርጋቸዋል፡፡ አትክልተኛው እንደሚያደርገው ይህንን የሚተላለፉ አንዳንድ ሰዎችን በሌሎች የማህበረሰብ አባላት ዘንድ ጤነኛ አይደሉም፣ እነርሱን አትስሟቸው፣… ወዘተ እያለ በሰዎች ዘንድ ያሳቅቃቸዋል፡፡ የተለዩት ሰዎች በያዙት ከማህበረሰቡ የተለየ ዓይነት ሃሳብ ወይም ማህበረሰቡ ዘንድ ገዢ የነበሩትን ህግጋት የመተቼት እና አዳዲስ ሃሳቦች የማምጣት ልምድ የሚቀጥሉ ከሆነ ይገድላቸዋል፡፡ በዚህም ሂደት ማህበረሰቡ ከአያቶቹ እና ቅድመ አያቶቹ የተለየ የእውቀትም ሆን የህግጋት ለውጥ ሳያደርግ ይቀራል-ኑሮውም እንደድሮው ኋላ ቀርነቱን እንደጠበቀ ይቀጥላል፡፡

ተለይተው እንዳደጉ እፅዋት ሁሉ እነዚህ የተለዩ ሰዎች በለስ ቀንቷቸው የእነርሱ መኖር ጠቀሜታው እንጂ ጉዳቱ ያን ያህል መሆኑን የተገነዘበ ማህበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ ከሆነ አዲስ ነገሮችን ያፈለቁ ሰዎች የተቀረውን የማህበረሰብ ክፍል እንዲያስተምሩ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህም መልኩ አብዛኛው ማህበረሰብ የተሰጠውን ዓዕምሮ እንደተለዩት ሰዎች ሁሉ እንዲጠቀምበት ይሆናል፡፡ ማህበረሰቡም በአያቶቹ እና ቅድመ አያቶቹ የነበሩትን ማህበረሰብ ተኮር ህግጋት እና አስተሳሰቦች መጠየቅ ይጀምራል፡፡ ጠይቆም አያበቃም-የህግጋቱ እና አስተሳሰቦች እርሱ በሚኖርበት ዘመን ገዢ መሆን አለመሆን ይወስናል፡፡ በዚህም ሁኔታ ከድሮ የተሻለ የአኗኗር ዘይቤ፣ ከአያቶቹ የተሻለ የእውቀት እና የንቃት ደረጃ ወዘተ እያጎለበተ ምድርም ለአዳዲስ አባላቷ የተመቼት እየሆነች ትሄዳለች፡፡

ሰላማችን አይጉደል!

© ሹመት ጌታሁን

Advertisements